ስለ እኛ ማወቅ ከፈለጉ

እኛ በአለሙ ሁሉ ያለ አዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ ባህሉንና ታሪኩን እንደጠበቀ እንዲቆይ ለማስቻል በሙሉ ሞራል የተነሳሳን ወጣት ሞያተኞች ነን። በአሁኑ ወቅት ከ ፪፻፶፼ (2.5 ሚሊዮን) በላይ የሚሆን ህዝብ አማርኛ ቋንቋን ከኢትዮጵያ ውጭ ለመግባቢያነት እንደሚጠቀም ይገመታል።ይህ ቁጥር ባለፉት አስርት አመታት ከኢትዮጵያ በስደት በሚወጡት ሰዎች ምክንያት በፍጥነት አድጓል። ኢትዮጵያዊያን ማንነታቸውንና ባህላቸውን ለመጠበቅና ለተተኪው አዲስ ትውልድም ለማስተላለፍ ሁሌም ቢሆን ብርቱዎችና ጉጉዎች ናቸው። ሆኖም ግን ዘመናዊ የቋንቋና ባህል ማስተማርያ ቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ አይገኝም። ይህ ችግር በተለይ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ባልሆኑ ሐገሮች በሚኖሩት ላይ የበለጠ ይጎላል።

ይህ ችግር ይህን በሶስት ቋንቋዎች ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀውን ዲቪዲ እንድናዘጋጅ አነሳስቶናል። የእኛ ዓላማ ከሀገር ውጪ ባለው ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ህጻናቶችን ዘመናዊ፣ መስህብነት ያለውና አሳታፊ በሆነው የአማርኛ መማርያ ቁሳቁስ እንዲማሩ ማስቻል ነው።

ይህ ዲቪዲ በማደጎ ልጅነት ኢትዮጵያዊያን ህጻናቶችን ለሚያሳድጉ ቤተሰቦች፣ ለሀገር ጎብኝዎች፣ ለንግዱ ማህበረሰብ ፣ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሰሩ ዲፕሎማቶች እና ተቀማጭነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሆኑ በትርፍ ላይ ባልተመሰረተ የበጎ አድራጎት ስራ ለተሰማሩ ሰራተኞች በጣም ጠቃሚ ነው።

ይህንን ልዩ የሆነ የአማርኛ እና ባህል ማስተማርያ ዲቪዲ እንደሚዎዱት እንተማመናለን። የእርስዎ ጠቃሚ የሆነ አስተያየትና እርማት ለኛ ስራ መቃናት ከፍተኛ ዋጋ አለው። ልጅዎት በትውልድ ሐገራቸው ኢትዮጵያ ሲሄዱ ለማህበረሰቡ ባዕድ እንዲሆኑ እንደማይፈቅዱ እርግጠኞች ነን።